ልክ የዛሬ 49 አመት ታህሳስ 3 1960 አመተ ምህረት አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ‹‹ወይዘሪት አዲስ አበባ›› የሚል አክሊል ደፋች፡፡ በወቅቱ ገና ታዳጊ ወጣት የነበረችው ይህች ቆንጆ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ላይ እንዲሁም ‹‹መነን›› መጽሄት ላይ ታሪኩዋ ወጣ፡፡ የማርቼዲስ እና የ50,000 ብር ሽልማት ወሰደች ተባለ፡፡ ከአመት በፊት የቆየ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳገላብጥ ይህን ዜና ወይም ታሪክ አነበብኩ፡፡‹‹ወሰኔ ሀይሉ የአዲስ አበባ ቆንጆ ተባለች›› ወይም ወይዘሪት አዲስ አበባ ተባለች ይላል ዜናው፡፡ እኔም ይህች ወጣት በአሁኑ ሰአት የት እና በምን ሁኔታ ላይ ትሆን;? ስል ራሴን ጠየቅኩ፡፡ መቼም ታሪክ እንደምወድ ታውቃላችሁ፡፡ እና ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉን መፈለጌን ቀጠልኩ፡፡ ፍለጋው በመጨረሻ ተሳካ፡፡ ሰኞ ታህሳስ 3 2009 ዛሬ ከሰአታት በፊት ወይዘሮ ወሰኔን በስልክ አገኘሁዋት፡፡ ‹‹ወይዘሮ ወሰኔ ልክ የዛሬ 49 አመት ታህሳስ 3 በዚህ ቀን ወይዘሪት አዲስ አበባ ተብለሽ ዘውድ ደፍተሸ ነበር፡፡ በቅድሚያ እንኩዋን ለዚህ ታሪካዊ ቀን አደረሰሽ፡፡›› አልኩዋት፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ቀኑን በማስታወሴ አመስግና ታሪኩን ልታጫውጠኝ ቀጠሮ ያዝን፡፡ ያኔ ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ አንድ ቆንጆ ምስል ላከችና ለውድድሩ ቀረበች፡፡ይህን የልጅነት ምስል ለዚህ ጽሁፍ ጋር አለ፡፡ መመልከት ይችላሉ፡፡ ግን ለውድድሩ ያን ያህል ትኩረት አልሰጠችም ነበር፡፡ መጠነኛ ፍርሀት ነበረባት፡፡ ቢሆንም ማበላሸት የለብኝም ብላ ስላመነች መድረኩ ላይ ወጣች፡፡ በጊዜው የክብር እንግዳ የነበሩት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሂልበርት አንፍሬ በአዳራሹ ነበሩ፡፡መጀመሪያ ለወይዘሪት አዲስ አበባ 52 ልጆች ነበሩ የተመረጡት፡፡ ከዚያ 12 ልጆች ለፍጻሜ ቀረቡ፡፡ በተለያየ ልብስ መድረኩ ላይ የወጡት እነዚህ ቆንጆዎች በምስሉ ላይ እንደሚታዩት በጣም ያምሩ ነበር፡፡ በመጨረሻ አሸናፊው የሚነገርበት ሰአት ደረሰ፡፡ የ12ቱ ልብ መምታት ጀመረ ፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉም የልብ ትርታዋ መጨመሩን ዛሬ ታስታውሳለች፡፡ በጊዜው ዳኛ ከነበሩት መካከል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርስ ና ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ይገኙበታል፡፡ በጊዜው ወይዘሮ ወሰኔ 23 ቁጥር ነበረች ፡፡ እናም 23 ቁጥር አሸናፊ ተብሎ ተጠራ፡፡ ታዳጊ ወሰኔ ግን 23 ቁጥር ሲጠራ በወጉ አልሰማችም ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ማሸነፏን ሲነግሩዋት ደስታዋ አየለ፡፡በጊዜው የማርቼዲስ ኩባንያ ፕሮሞሽን እየሰራ ስለነበር ለአሸፊዎቹ ማርቼዲስ ሸለመ፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉ ዛሬ በ60ዎቹ መጀመሪያ ላይ ትገኛለች፡፡ የዛሬ 49 አመት ወደ ባህር ማዶ አቅንታ የነበረችው ወሰኔ ዛሬ በሀገርዋ ላይ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ አንድ ነገር ለማስቀመጥ እየሰራች ነው፡፡ የማሰልጠኛ ማእከል ከፍታም ህልሙዋን እያሳካች ትገኛለች፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ በአስፋወሰን እና በመነን እንዲሁም በእንግሊዝ ስኩል የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱዋን ተከታትላለች፡፡ ወይዘሮ ወሰኔን ዛሬ ከሰአታት በፊት ሳወራት ያን ጊዜ የነበረው ሽልማት የሞዝቮልድ እቃም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹50ሺህ ብር ተሸለምኩ›› ስትለኝ ግን የበለጠ ተገረምኩ፡፡ ያኔ 50ሺህ ብር ቀላል ብር አልነበረም፡፡ ወሰኔ ግን ያንን ብር ለወላጆችዋ መስጠትዋን ታስታውሳለች፡፡ እንዲያውም በስሙዋ አካውንት ተከፍቶላት ነበር፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉ ለወላጆችዋ 3ኛ ልጅ ነች፡፡ አባትዋ አቶ ሀይሉ ባህሩ ሲባሉ ወላጅ እናትዋ ደግሞ ወይዘሮ ጸሀይነሽ አንዳርጌ ይባላሉ፡፡ ለዚህ ደረጃ ትደርስ ዘንድ የወላጅ ሚና ትልቅ ነበር፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉ ከዛሬ 49 አመት በፊት ታዳጊ ሳለች የተነሳችውን ምስል እነሆ እንዲመለከቱ ብያለሁ፡፡
ደግሞ ዘንድሮ 60ዎቹ ላይ የተነሳችውን ማየት ይችላሉ፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ከበፊት አንስቶ በፋሽን ላይ ለመሰማራት ትፈልግ ነበር፡፡ ይህን ህልሙዋን ለማሳካት ባለፉት 41 አመታት በጀርመንና በአሜሪካ ስለ ፋሽን ዲዛይን በትልቅ ደረጃ ተምራለች፡፡ ወደ ሀገር ቤት የመጣችው በ2002 ነበር፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ስለ ፋሽን 㙀አስተምራለች፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ሀይሉ ከጀርመናዊ ባለቤቷ 2 ልጆችን ወልዳለች፡፡ በስራዋም በህይወትዋም ደስተኛ ነች፡፡ ወይዘሮ ወሰኔ ጽሁፌን ለማጠናከር የሚረዳኝን ወደ 10 የሚጠጋ ምስል ሰጥታኛለች፡፡ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ስለ ፋሽን ኢንዱስትሪው የምትለውን ይዘን ልንቀርብ እንሞክራለን፡፡ የሁዋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና ብሂሉ ወይዘሮ ወሰኔን እንኩዋን አደረሰሽ ማለትን እወዳለሁ ፡፡
1 Comment
|
CategoriesArchives |